August 18, 2026 ዜና (News)
  • 7
  • በዓለ ደብረ ታቦር

    በዓለ ደብረ ታቦር

    " ነቢዩ ዳዊት ከተራሮች ከፍ ከፍ ባደረጋት
    በኪሩቤል አምሳል በመሰላት
    በሩቅ ሰማይ ጥግ በደብረ ታቦር
    የቃል ኪዳን ራስ ክርስቶስ በተገለጠባት ጊዜ
    እነሆ ጴጥሮስ በመካከሏ
    ማደሪያ ይሠራ ዘንድ ተመኘ "
    ነግሥ ዘደብረ ታቦር

    በዓለ ደብረ ታቦር ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከምታከብራቸው ዘጠኙ ዐበይት የጌታ በዓላት መካከል አንዱ ነው ምን አድርጎበታል ቢሉ ብርሃነ መለኮቱን ለሐዋርያት ገልጾበታል ታቦር የተራራ ስም ነው ጌታ በመዋዕለ ስብከቱ ብዙውን ጊዜ የሚያስተምረው ተአምራት የሚያደርገው በተራራ ላይ ነበር በዚህም ዕለት ዘጠኙን ከእግሩ ደብር ትቶ ሶስቱ ጴጥሮስን ዮሐንሰንና ያዕቆብን አስከትሎ ከርእሰ ደብር ወጣ በዚያም
    " በፊታቸውም ተለወጠ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ ።እነሆም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው ። ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን ጌታ ሆይ ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን  ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንስራ አለ ።እርሱም ገና ሲናገር፥ እነሆ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው እነሆም ፥ ከደመናው  በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው ፤ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ።”ማቴ 16፣1-5

    በዚህ በዓል በተዋሕዶ የከበረ፣ አምላክ ሲሆን በፈቃዱ የሰውን ባሕርይ ያለመለወጥ የተዋሐደ ጌታ መለኮታዊ ክብሩ፣ የተዋሕዶው ፍጹምነት ይነገርበታል፣ የነቢያትና የሐዋርያት ምስክርነት ይተረጎምበታል፡፡ በባሕላዊ ገጽታው ይህ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ዘንድ ‹ቡሄ› በመባል ይታወቃል፡፡ ቡሄ ማለት ‹መላጣ፣ ገላጣ› ማለት ነው፡፡ ክረምቱ፣ ጭጋጉ፣ ደመናው ተወግዶ የብርሃን ወገግታ የሚታይበት በዚሁ በዓል አካባቢ ስለሆነ  ‹‹ቡሄ›› ተብሎ ይጠራል፡፡ በዓለ ደብረ ታቦር ጌታችን ምሥጢረ መለኮቱን የገለጠበት፤ ብርሃን የታየበትና ድምፀ መለኮቱ የተሰማበት ዕለት ስለሆነ ‹‹የብርሃን በዓል›› ይባላል፡፡

    የደብረ ታቦር ተራራ ከገሊላ ባሕር በምዕራባዊ በኩል 10 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኝ  ሲሆን፤ ከፍታው ከባሕር ጠለል በላይ 572 ሜትር ያህል ነው፡፡ በዚህ ተራራ ላይ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን እንደሚገልጽ አስቀድሞ ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ “ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል” ብሎ ተናግሮ ነበር (መዝ. 88፥12)፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ተራራ ላይ ብርሀነ መለኮቱን በመግለጡ ተራሮችም የፈጣሪያቸውን ተዓምራት በማየታቸው የነቢያት ትንቢት ተፈጽሟል፡፡
    ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን በደብረ ታቦር የገለጠው ከተስእሎተ ቂሣርያ በ6ኛው ቀን (ነሐሴ 13 ቀን) ነው፡፡
    ♦  ተራራ የወንጌል ምሳሌ ናት፡፡ ተራራ ሲወጡት ያስቸግራል፤ ከወጡት በኋላ ግን ከታች ያለውን ሁሉ ሲያሳይ ደስ ይላል፡፡ ወንጌልም ሲማሯት ታስቸግራለች፡፡ ከተማሯት በኋላ ግን ጽድቅንና ኃጢአትን ለይታ ስታሳውቅ ደስ ታሰኛለች፡፡
    ♦ ተራራ የመንግስተ ሰማያት ምሳሌ ነው፡፡ ተራራን በብዙ ጻዕር እንዲወጡት መንግስተ ሰማያትንም በብዙ መከራ ያገኟታልና፡፡ (ሐዋ.14፡22)
    ♦ ተራራ የቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ በደብረ ታቦር ምስጢረ ሥላሴ እንደተገለጠ በቤተ ክርስቲያንም የቅድስት ሥላሴ አንድነትና ሦስትነት ይነገርባታልና፡፡ ተራራ መሠረቱ ከመሬት አናቱ ከሰማይ እንደሆነ ሁሉ፤ ቤተ ክርስቲያንም መሠረቷ በምድር ሲሆን ራሷ (ክርስቶስ) በሰማይ ነውና፡፡ የቤተክርስቲያን አገልጋዮቿ የተጠሩት ከምድር (ከዓለም) ሲሆን ክብራቸው ግን በሰማይ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እኛስ ሀገራችን በሰማይ ነውና›› እንዲል (ፊልጵ. 3፥20)፡፡ በዚህም መነሻነት ጌታችን በልዩ ልዩ ኅብረ አምሳል ለደቀመዛሙርቱ ነገረ ተዋሕዶውን አስረዳቸው፡፡ ደቀመዛሙርቱም ዛሬ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን እንደምታምነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ ሲሆን ሰው መሆኑን አመኑ፣ መሰከሩ፡፡

    ፨ መልኩ ተለወጠ፤ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ

    ሦስቱ ሐዋርያት በተራራው ሳሉ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሲጸልይ ሳለ መልኩ በፊታቸው ተለወጠ፡፡ ይህም የመለኮቱን ብርሃን ሲገልጥ ነው እንጂ ውላጤ/መለወጥ አይደለም፡፡ “እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም” እንዳለ /ሚል 3፥6/ በእርሱ ዘንድ መገለጥ እንጂ መለወጥ የለም፡፡ ሦስት ክንድ ከስንዝር አካል ምሉዕ ብርሃን ሆኗል፡፡ ይህም አበቦች ከአዕጹቃቸው እንዲፈነዱ ያለ መገለጥ ነው፡፡ ፊቱም እንደ ፀሐይ ብሩህ ሆነ፡፡ ልብሱም እንደ በረድ ጸዓዳ ሆነ፡፡ ይህ ሁሉ ነገረ ተዋሕዶን እንዲረዱ የተደረገ መገለጥ ነው፡፡ ሰውነቱን አልካዱም፣ አምላክነቱን ግን ተጠራጥረው ነበርና አምላክነቱን ከሰውነቱ አዋሕዶ ነገረ ተዋሕዶን ገለጠላቸው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ማቴዎስ፣ በወርኃ ነሐሴ በዕለተ እሑድ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን ገልጧል፡፡

    ፨ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው

    መጽሐፍ ቅዱስ ሙሴና ኤልያስ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሲነጋገሩ ለቅዱሳን ሐዋርያት እንደታዩአቸው ይነግረናል እንጅ የተነጋገሩትን ዝርዝር አላስቀመጠልንም (ማቴ. 17፡3)። ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት በትውፊት የከበሩ ናቸውና ከቅዱሳን ሐዋርያት በቃል የተማሩትን የሙሴና የኤልያስ ምስክርነት አቆይተውልናል ከሞተ ብዙ ዘመን የሆነውን ሙሴን ከመቃብር አስነስቶ ቀጥሎም በእሳት ሠረገላ ያረገውንና በብሔረ ሕያዋን የሚኖረውን ኤልያስን ወደ ደብረ ታቦር እንዲመጡ ያደረገበት ምክንያት እርሱ የባሕርይ አምላክ መሆኑን እንዲመሰክሩ ነው፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከመቃብር ተነሥቶ “እኔ ባህር ብከፍልም፤ ጠላት ብገድልም፤ ደመና ብጋርድም፤ መና ባወርድም እንደ እስራኤልን ከክፋታቸው መልሼ ማዳን ያልተቻለኝ ደካማ ነኝ፤ የእኔን ፈጣሪ እንዴት ሙሴ ይሉሃል? የሙሴ ፈጣሪ እግዚአብሔር ይበሉህ እንጂ!” ብሎ ስለጌታችን አምላክነት ምስክርነት ሰጥቷል፡፡

    በአጠቃላይ በወንጌሉ ያመንንና በስሙ የተጠመቅን ክርስቲያኖች የደብረ ታቦርን በዓል ስናከብር ቅዱስ ጴጥሮስ “ለእኛ በዚህ መኖር መልካም ነው” እንዳለው በደብረ ታቦር በምትመሰለው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነን የቤተ ክርስቲያናችን ሕግና ሥርዓት አክብረን፣ በምግባር በትሩፋት አጊጠን ሊሆን ይገባል።
    መልካም በዓል