ነሐሴ 7 ጽንሰታ ለማርያም
ነሐሴ 7 ጽንሰታ ለማርያም
" አሁንም የእግዚአብሔር የጸጋ ልጆችና የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ማህበሮች ሆይ ይኽቺን የተባረከችና የተመረጠች ሙሽራ የወለዱልንን ኢያቄምንና ሐናን እናመስግናቸው የማትነቀፍ የእስራኤል ድንግልን የተባረከችዋን ፍሬ ያፈራችበትን ንጽሕት የምትኾን የሩካቤያቸው ዕለት እንደምን ያለች ዕለት ናት? ከይሁዳ ወገን ለኾነችው ንጽሕት ርግብ መፀነስ በእግዚአብሔር ፈቃድ የተደረገ የጾታዊ ተዋሕዷቸው ቀን ይኽቺ እንዴት ያለች የተመረጠች ቀን ናት፤ ለንጉሥ ማደሪያ አዳራሽ መመሥረት የተደረገባት የደስታ ቀን እንዴት ያላች ቀን ናት "
አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ/መጽሐፈ አርጋኖን
ነሐሴ ሰባት በዚች ቀን እግዚአብሔር የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤልን ወደ ከበረና ከፍ ከፍ ወዳለ ጻድቅ ኢያቄም ላከው አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያምን ፅንስቷንና ልደቷን በእርሷም ለዓለሙ ሁሉ ድኅነትና ተድላ ደስታ እንደሚሆን ነገረው።
ይህ ጻድቅም ሰው ኢያቄምና የከበረች ሚስቱ ሐና ልጅ ሳይወልዱ ሸመገሉ የከበረች ሐና መካን ሁናለችና ስለዚህም እጅግ ያዝኑ ነበር የእስራኤል ልጆች ልጅ ያልወለደውን ከእግዚአብሔር በረከትን ያጣ ነው እያሉ ያቃልሉት ነበርና ። እነርሱም ልጅን ይሰጣቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ዘወትር ፈጽሞ ይለምኑ ነበር ። ከዚህም በኋላ ወንድ ልጅን ወይም ሴት ልጅን ቢወልዱ ለእግዚአብሔር ቤት አገልጋይ ሊያደርጉ ስለትን ተሳሉ።
የከበረ ኢያቄምም በተራራ ላይ ሳለ ሲጸልይና ሲማልድ እነሆ በላዩ እንቅልፍ እንቅልፍ ብሎት አሸለበ ያን ጊዜ ከእግዚአብሔር የተላከ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ተገለጸለት እንዲህም አለው ሚስትህ ሐና ትፀንሳለች ዓለሙ ሁሉ ደስ የሚሰኝባትን የብዙዎችም ዐይነ ልቡ ናቸው በእርሷ የሚበራላችውን በእርሷም ድኅነት የሚሆንባትን ሴት ልጅን ትወልድልሃለች።
በነቃ ጊዜም ወደ ቤቱ ሒዶ ለሚስቱ ለቅድስት ሐና ነገራት ራእይዋን እውነት እንደሆነች አመኑዋት ከዚህም በኋላ ነሐሴ ሰባት በዚች ቀን የከበረች ሐና ፀነሰች ለዓለም ሁሉ መመኪያ የሆነች በሁለት ወገን ድንግል የሆነች የአምላክ እናት እመቤታችንን ማርያምን ወለደቻት።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ኢያቄምና ሐና ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።